ድርጅቶቹ የልማት አጋርነታቸውን የሚያጠናክሩበት አደረጃጀት ተመሠረተ (አዲስ ዘመን ጋዜጣ)

Details
Published Date
Written By ለምለም መንግሥቱ

የፌዴራል የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ፎረም በኢትዮጵያ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የልማት አጋርነታቸውን ለማጠናከር የሚያስችል አደረጃጀት ፈጥሮ እየሰራ መሆኑን ገለጸ፡፡ የፌዴራል የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ፎረም ፕሬዚዳንት አቶ ነጋሽ ተክሉ ፎረሙ ትናንት በደሳለኝ ሆቴል ባካሄደው ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ እንደገለጹት፤ ፎረሙ በኢትዮጵያዊነት፣ በኢትዮጵያ ነዋሪነትና በዓለም አቀፍ ህጋዊነት ተመዝግበው በልማት ተግባር በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙት የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አንድ ዓላማ ይዘው ለልማቱ የበለጠ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱበት አደረጃጀት ፈጥሯል፡፡

የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ለአንድ ዓላማ በመንቀሳቀስ በጋራ ድምጻቸውን የሚያሰሙበት አደረጃጀት ሲፈጠር የመጀመሪያ መሆኑን የገለጹት አቶ ነጋሽ፤ ፎረሙ ድርጅቶቹ ከመንግሥት ጋር ተቀራርበው የሚሰሩበት መድረክ እንደሚፈጥርም ተናግረዋል። በተለይም ለልማት ያላቸው አጋርነት የበለጠ ጎልቶ እንዲወጣና ግባቸውን እንዲያሳኩ አስፈላጊ ድጋፎችን እንደሚያደርግ ጠቁመው፤ ከለጋሽ ድርጅቶች ሊያገኙ የሚችሉትን ድጋፍ በማመቻቸት ደረጃም እገዛ እንደሚያደረግ አስረድተዋል፡፡ «ፎረሙ ከተቋቋመ አጭር እድሜ ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከውስጥ አደረጃጀት ጀምሮ በፎረሙ የመተዳደሪያ ደንብ፣ የመለያ ምልክት በመሳሰሉት ላይ በመወያየት መደራጀት ይጠበቅበታል» ያሉት አቶ ነጋሽ፤ የሁለተኛ ጉባኤው በነዚሁ ላይ ተነጋግሮ መስመር የማስያዝ ዓላማ እንዳለው አመልክተዋል፡፡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ መሰረት ገብረማርያም እንዳስረዱት፤ ፎረሙ ከኤጀንሲው አስተዳደራዊ እውቅና አግኝቷል፡፡

በመንግሥትና በዘርፉ መካከል እንደድልድይ ሆኖ ለማገልገል የተቋቋመ ነው፡፡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የሚያሰባስቡት ሀብት ለችግር የተጋለጡ የህብረተሰብ አካላትን ማኅበራዊ ችግሮች ለማቃለል እንደሆነ ያወሱት አቶ መሰረት፤ ቀደም ባሉት ጊዜያት በአንዳንድ ድርጅቶች በኩል በተገቢው መንገድ ያለማገልገል፣ አላግባብ ለመበልጸግ ጥረት ማድረግ፣ ብክነትና በጎ ተግባርን ከፖለቲካው ጋር የመደበላለቅ ሁኔታ እንደነበር አመልክተዋል፡፡ አሁን ግን ህጉን ተከትሎ መስራትና ህብረተሰቡን የማገልገል አስተሳሰብ እየዳበረ መምጣቱን ገልጸው፤ እነዚሀን ጅምር በጎ ተግባራት ማጠናከር እንደሚገባ አስታወቀዋል፡፡

ኤጀንሲው ከምዝገባ ሂደት ጀምሮ ድርጅቶቹ ችግር ሲያጋጥማቸው የማስተካከያ ሥራ እስከመስራት እንደሚደግፋቸው አስታውቀዋል፡፡ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ልዩ ረዳትና የሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግደይ ዘሪሁን ሚኒስትሩን ወክለው በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ለልማቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸውን አመልክተው፤ ፎረሙ በጎ ተግባሩን በማጠናከር መጥፎዎቹን በማስወገድ ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

Share it now!
Published Date
Written By ለምለም መንግሥቱ

የፌዴራል የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ፎረም በኢትዮጵያ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የልማት አጋርነታቸውን ለማጠናከር የሚያስችል አደረጃጀት ፈጥሮ እየሰራ መሆኑን ገለጸ፡፡