ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የሥራ ፈቃድ ማደስ ባልቻሉ ተቋማት ጉዳይ ከመንግሥት ጋር ሊነጋገሩ ነው (ሪፖርተር ጋዜጣ)

ኢትዮጵያ ውስጥ እየሠሩ የሚገኙ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ያቋቋሙት አገር አቀፍ መድረክ፣በሥራ ላይ የዋለው የ70/30 መመርያ በፈጠረባቸው ችግር ምክንያት የሥራ ፈቃድ ማደስ ባልቻሉ ተቋማት ጉዳይ ላይ ከመንግሥት ጋር ለመወያየት እየተዘጋጁ ነው፡፡

የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ በቅርቡ ያወጣው የ70/30 መመርያ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበር፣ የአካል ጉዳተኛ ማኅበራትና የጤና ባለሙያዎች ማኅበር የሥራ ፈቃዳቸውን እንዳያድሱ ተፅዕኖ ፈጥሮባቸዋል ተብሏል፡፡ ምክንያቱም በእነዚህ ዘርፎች ሥራዎችን ሲያካሄዱ የቆዩት እነዚህ ማኅበራት ወጪያቸውን ሸፍነው የቆዩት 10 በመቶ ከአባላት መዋጮ፣ ቀሪውን 90 በመቶ የሚሸፍኑት ከዕርዳታ ድርጅቶች በሚያገኙት ገንዘብ ነበር፡፡ ነገር ግን አዲሱ መመርያ  የቀድሞ ሥሌት ተገላቢጦሽ በመሆኑ ማኅበራቱ ዳግም ወደ ሥራ እንዳይገቡ እንቅፋት ሆኗል በሚል ቅሬታ ሲነሳ ቆይቷል፡፡

በግንቦት 2005 ዓ.ም. ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ ከዚያ ወዲህ ባሉት ስምንት ወራት ውስጥ ራሱን በማደራጀት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ የፌደራል በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት መድረክ ፕሬዚዳንት አቶ ነጋሽ ተክሉ እንደገለጹት፣ መድረኩ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ነው፡፡በጎ አድራጎት ድርጅቶቹ በራሳቸው በኩል ያሉባቸውን ችግሮች እንዲያስተካክሉ፣ መንግሥትም ማስተካከል ያለበትን እንዲያስተካክል፣ እንዲሁም ለእነዚህ ተቋማት የሽግግር ጊዜ እንዲሰጥ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ድረስ እንደሚኬድ አቶ ነጋሽ ገልጸዋል፡፡ይህንን መድረክ ያቋቋሙት በኢትዮጵያ የተለያዩ ምግባረ ሰናይ ሥራዎችን በመሥራት ላይ የሚገኙት ሦስት ሺሕ ተቋማት ናቸው፡፡

መድረኩ ባለፈው ማክሰኞ ሁለተኛውን መደበኛ ጉባዔ በደሳለኝ ሆቴል አካሂዷል፡፡ ይህ መድረክ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ ወጪን በመጋራት፣ የበጎ አድራጎት አገልግሎት አሰጣጥ ሁኔታን ለመወሰን ያወጣውን መመርያ በበጎ መንፈስ ተመልክቶታል፡፡አቶ ነጋሽ እንደገለጹት፣ በነፃ የሚቀርብ አገልግሎት የጠባቂነት ስሜት ስለሚፈጥርና ኅብረተሰቡ የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማው ለማድረግ መመርያው አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ነገር ግን ከመድረኩ አባላት በመመርያው ውስጥ የተከተቱ አንዳንድ ነጥቦች እንዲሻሻሉላቸው የሚፈልጓቸው ነጥቦች በመኖራቸው፣ መድረኩ በቀጣይነት ከኤጀንሲው ጋር እንደሚወያይበት አቶ ነጋሽ ጠቁመዋል፡፡ ይህ መመርያ አንድ የበጎ አድራጎት ድርጅት ለሚያከናውናቸው ተግባራት ተጠቃሚ የሆነው የኅብረተሰብ ክፍል እስከ 25 በመቶ የሚጠጋ ሀብት ማበርከት እንዳለበት ይደነግጋል፡፡

Share it now!